የኢትዮጵያ ሠራዊት የኬንያን አውሮፕላን በስህተት መትቶ መጣሉን አመነ

የኢትዮጵያ ሠራዊት የኬንያን አውሮፕላን በስህተት መትቶ መጣሉን አመነ

የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያ ውስጥ የኬንያን የጭነት አውሮፕላን መትቶ መጣሉን በሶማሊያ የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል – አሚሶም አስታወቀ።

የአሚሶም ኃይል አባል አይደለም የተባለው የኢትዮጵያ ሠራዊት ሶማሊያ ውስጥ አውሮፕላኑን መትቶ የጣለው ከአጥፍቶ ጠፊ ተልዕኮ ጋር ተመሳስሎበት ነው ተብሏል። አምስት ሰዎችን ጭኖ ሲበር የነበረ አውሮፕላን በሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት የተመታው ሰኞ ሚያዚያ 26/2012 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ነበር። አውሮፕላኑ ባርዳሌ በምትባል ከተማ በሚገኝ አየር ማረፊያ አቅራቢያ የተመታ ሲሆን የሁሉም ተሳፋሪዎች ሕይወት አልፏል።

አውሮፕላኑ ተመቶ የወደቀበት ቦታን ተቆጣጥሮ የሚገኘው የአሚሶም ሴክተር ሦስት ኃይል ኮማንደር የሆኑት ብርጋዲዬር ጀነራል አለሙ አየነ እንዳሉት ጦራቸው ስለ በረራው ቀድሞ መረጃ እንዳልነበረው እና አውሮፕላኑ ለማረፍ የሄደበት አቅጣጫ አጠራጣሪ ስለነበር ተመትቷል ብለዋል።

በአካባቢው በሚገኘው አየር ማረፊያ አንድ አውሮፕላን ለማረፍ የሚሄድበት አቅጣጫ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ሲሆን፤ ይህ በኢትዮጵያ ጦር ተመትቶ የወደቀው አውሮፕላን ግን ለማረፍ ሲበር የነበረው በተቃራኒ አቅጣጫ ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ነበር ተብሏል።

ብርጋዴየር ጀነራል አለሙ አየነ በባርዳሌ የጦር ካምፕ ጥበቃ ላይ ያለው ጦራቸው አውሮፕላኑን መትቶ የጣለብትን ሦስት ምክንያቶች ገልጸዋል።

አውሮፕላኑ ወደ ባርዳሌ ከተማ እንደሚበር መረጃ እንዳልነበራቸው፣ አውሮፕላኑ ከተለመደው ውጪ ወደ ምድር ቀርቦ እየበረረ እንደነበር እንዲሁም በካምፑ የሚገኘው ጦር አውሮፕላኑ ከተለመደው ውጪ ዝቅ ብሎ የሚበረው የአጥፍቶ መጥፋት ዒላማ እየፈለገ እንደሆነ በመረዳታቸው መትተው መጣላቸውን አስታውቀዋል።

እንደ አሚሶም መግለጫ ከሆነ አውሮፕላኑ ለማረፍ ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ ለሁለተኛ ጊዜ ለማረፍ ሙከራ ሲያደርግ መመታቱ ተጠቁሟል።

የአፍሪካ ሕብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ-አሚሶም እንዳለው አውሮፕላኑ ምንም እንኳ አየር ላይ ሳለ በኢትዮጵያ ሠራዊት ቢመታም፤ ለማረፍ በሚያደርገው ጥረት በጣም ወደ ምድር ተጠግቶ እየበረረ ስለነበረ ጎማዎቹን ለመዘርጋት በቂ ጊዜ ስለማይኖረው ያለችግር የማረፍ እድል አልነበረው ብሏል።

አሚሶም በመረጃ ክፍተት አውሮፕላኑ ተመቶ ወድቋል ካለ በኋላ አውሮፕላኑ ከአሚሶም ውጪ ባሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች መመታቱን አስታውሷል።

አሚሶም በመግለጫው በጉዳዩ ላይ ዝርዝር እውነታውን ለማወቅ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ መንግሥታት በጣምራ በአደጋው ዙሪያ ምርመራ እንዲያደርጉ ጠይቋል።

የሶማሊያ ደቡብ ምዕራብ ምክትል የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ሐሳን ሁሴን ለቢቢሲ እንደገለጹት ከአምስቱ ሟቾቹ መካከል ሁለቱ ሶማሊያውያን ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ ኬንያውያን ናቸው።

ንብረትነቱ የአፍሪካን ኤክስፕረስ ኤርዌይስ የሆነው አውሮፕላን አደጋ እንዳጋጠመው በተነገረበት ወቅት በርካቶች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በኢትዮጵያ ጦር ተመትቶ መውደቁን ገልጸው የነበረ ቢሆንም፤ ይህ በአሚሶም፣ በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ መንግሥታት ሳይረጋገጥ ቆይቷል።

የአፍሪካን ኤክስፕረስ ኤርዌይስ የኬንያ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሲሆን ዋና መቀመጫው በመዲናዋ ናይሮቢ ነው።

አውሮፕላኑ ንብረትነቱ የአፍሪካን ኤክስፕረስ ኤርዌይስ የተባለ የኬንያ አቪዬሽን ድርጅት እንደሆነና በወቅቱ የሰብዓዊ እርዳታ ቁሳቁሶች የሆኑ መድሃኒቶችንና የወባ መከላከያ አጎበር ጭኖ እንደነበር ተገልጿል። [BBC Amharic]