የግድቡ ጉዳይ፡ ለጊዜያዊ ፕሮፓጋንዳ ብሄራዊ ጥቅም እንዳይጎዳ

grand ethiopian renaissance dam

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረግ የነበው ድርድር ከተቋረጠ ወዲህ በግብጽ እና ኢትዮጲያ መካከል የዲፕሎማሲ እና የፕሮፓጋንዳ ጦርነት በአዲስ መልኩ አገርሽቶበታል። በቅርቡ በተደረገው የገዢው ፓርቲ ስብሰባ ላይ የተነሳው ይህ ጉዳይ ከምርጫው ጋር “ግብጽ ጦርነት ልታውጅብን ነው” በሚል ለህዝብ ቅስቀሳ እንደሚጠቅም ተነግሯል። የገዢው ፓርቲ ባላንጣዎች እና ተቃዋሚዎችን ለመምታትም ይረዳል በሚል ስልት ተቀይሷል። በዚያ ስብሰባም ሆነ ከዚያ በኋላ የፓርቲው አመራር እና ካድሬዎች ለፕሮፓጋንዳ ዘመቻ እያሟሟቁ ነው። “ባንዳ” እና “የግብጽ ተላላኪ” የሚሉ ቃላቶች ካሁኑ ሲወረወሩ እየሰማን ነው። እስቲ ለጊዜው የፕሮፓጋንዳውን ጉዳይ ወደጎን ትተን በቅርቡ ላገረሸበት አምባጓሮ እንዴት ደረሰን የሚለውን እንይ?

የኢትዮጲያ እና የግብጽ ውዝግብ ከሁለት ለማስታረቅ ከባድ ከሆኑ እውነታዎች የመነጨ ነው። ይህም የናይል ወንዝ አብዛኝው ውሀ ከኢትዮጲያ ተራሮች መፍለቁ እና አብዛኛውን ውሀ የምትጠቀመው ግን ግብጽ መሆኗ ነው።

ግብጽ በውሃዉ የመጠቀም የበላይነቷን ህጋዊ ከለላ ለመስጠት በ1959 ከሱዳን ጋር ውል ተፈራረመች። ውሉ አብዛኛውን ውሃ ለግብጽ፣ የተወሰነውን ለሱዳን በማከፋፈል ለኢትዮጲያ ግን ጠብታ ዉሃ አልሰጠም ነበር። እናም ግብጽ ይህንን ስምምነት እንደ ከለላ ብታቀርበውም ኢትዮጲያ ግን አልተቀበለችውም።

ለዘመናት ይህን ኢፍትሃዊ ስምምነት በፍትሃዊ ስምምነት ለመተካት የተደረጉ ውይይቶች እና ድርድሮች ውጤታማ አልነበሩም። ኢትዮጲያ ባልፈረመችው ስምምነት ከምድሯ በሚፈልቀው ውሃ የመጠቀም መብቷን ለማረጋገጥ ብትሞክርም በግብጽ ጫና እስካሁን አልተሳካም። ግብጽ ኢትዮጵያ ውሃውን እንዳትጠቀም የታወቁ እና ለዘመናት በስራ ላይ የዋሉ ሶስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎችን ትጠቀማለች።

1) የኢትዮጵያን የውስጥ ፀጥታ ማወክ:-

በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉ ፖሊቲካዊ ግጭቶች ዉስጥ (በተለይ በመንግስት እና በአማጺያን) የአንዱን ወገን በመደገፍ ጦርነት እንዲባባስ ማድረግ ነው። ኢትዮጲያ በውስጣዊ የፖሊቲካ ቀውስ እና ግጭት የምትታመስ ከሆነ በአባይ ውሃ ላይ መስራት ያለባትን መሰረተ ልማቶች ለማከናወን የገንዘብ አቅም እና የአመራር ትኩረቱም አይኖራትም ከሚል እሳቤ የመነጨ ስልት ነው። ደግሞም ለዘመናት ሰርቷል። ከነበረን ውስጣዊ የፖሊቲካ ቀውስ አንጸር ለዚህ ስልት በጣም ተጋላጭ ነበርን።

2) ኢትዮጲያን ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ማጋጨት:-

እንደዚይ አይነት ግጭት ወይም አለመስማማት ሲከሰት ግብጽ ከኢትዮጲያ ጋር የተጋጨውን ጎረቤት ሀገር በማበረታታ እና በመደገፍ ተቃርኖው ከተቻለ ወደ ግጭት አልያም ወደ ጦርነት እንዲያድግ ታደርጋለች። ልክ እንደ ውስጣዊ ግጭት ሁሉ ከጎቤት ሀገር ጋር የሚኖረው ተቃርኖም እትዮጲያ የአባይ ውሃ ለማልማት አቅሙ እና ትኩረቱ እንዳይኖራት ያደርጋል።

3) የአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በውሃ ነክ ፕሮጀክቶች ላይ ብድርም ሆነ እርዳታ ለኢትዮጲያ እንዳያደርጉ ማድረግ:-

ግብጽ በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ካላት ከፍተኛ ሚና እና የስዊዝ ካናል የባህር ንግድ ኮሪደር ከመቆጣጠሯ አንጻር በሃያላን ሀገራት እና የፋይናደስ ተቋማት ላይ ከኛ በበለጠ ጫና ማድረግ ትችላለች። አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ የአለም ባንክ እና IMF ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን ለማልማት የሚስፈጋትን ካፒታል እንዳይሰጧት ማድረግ ችላለች።

የግብጽ ጫና በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለሌላ ጉዳይ በዕርዳታም ሆነ በብድር ከነዚህ ሀገራት የሚመጣን ገንዘብ በአባይ ተፋሰስም ሆነ ከገባር ወንዞች ጋር ለተያያዘ ፕሮጀክት አንድ ሳንቲም እንዳንጠቀም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል። ይህ ደግሞ ደሃ ለሆነችው ኢትዮጵያ የአለም አቀፍ የፋይናንስ ምንጮችን ተጠቅማ የውሃ ሀብቷን እንዳታለማ ጋሬጣ ሆኗል። ለዚህ ነው የህዳሴ ግድብ በድብቅ ተጀምሮ ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ እና የህዝብ ርብርብ እንዲሰራ የተወሰነው።

ኢትዮጵያ በውስጣዊ የፖሊቲካ ቀውስ ስትታመስ መቆየቷ ፣ ከአንዳንድ ጎረቤቶቿ ጋር ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ውስጥ መግባት እና የኢኮኖሚ አቅሟ ያልተጠናከረ መሆኑ ለነዚህ የግብጽ ስትራቴጂዎች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ አድርጓት ቆይቷል።

ከሶስቱ የግብጽ ስትራቴጂዎች በጣም ጎጂው ነገር ግን ለማስቀረት ቀላል የሆነው የውስጥ ግጭቶችን ማስወገድ ነው። የውስጥ ግጭት አለ ማለት የድሃውን ኢኮኖሚ ይጎዳል። ለልማት መዋል ወይም መቆጠብ ሲገባው ለጦርነት ከሚወጣው ገንዘብ በተጨማሪ የመሰረተ ልማቶች መውደም እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መገደብ የፋይናንስ አቅማችንን ከማሳደግ ይልቅ እንዲመናመን ያደርገዋል። የሀገር መሪዎች ትኩረትም ከልማት ይልቅ ወደ ጦርነት እንዲዞር ያደርጋል። የሀገር ውስጥ ጦርነት ደግሞ ከጎርቤት ሀገሮች ጋር ያለንን ግንኙነትም ያሻክራል። ለዚህ ዋናዉ ምክንያት ደግሞ በሀገር ውስጥ የሚፈጠሩ አማጺያን የጎረቤት ሀገራትን ድጋፍ ማግኘታቸዉ እና እንደ መደበቂያም መጠቀማቸው አይቀሬ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በኛ ሀገር መንግስት እና በጎረቤት ሀገር መካከል ያለውን ግንኙነት እያሻከረው ይሄዳል፡፡ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ መሻከር ሶስተኛ ወገንን፣ ማለትም ግብጽን ይጋብዛል።

በሀገራችን ውስጥ የፖሊቲካ እና የደህንነት ቀውስ መፈጠር፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መበራከት እና ጠንካራ ቅቡልነት ያለው መንግስት አለመኖር በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ውስጥ ያለንን ተደማጭነት ይጎዳል። ይህ ግብጽ የአለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያን እንዳይረዱ ለምታደርገው ጫና ተጨማሪ ድጋፍ ይሆንላታል። እናም የውስጥ ፖሊቲካችንን ማስተካከል እና ከግጭት ማስወጣት የግብጽን ስትራቴጂ ለመቋቋም ወሳኝ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው።

የህዳሴው ግድብ ግብጽ በውስጣዊ ፖሊቲካ እየታመሰች ባለችበት ወቅት በድብቅ እና በፍጠነት የተጀመረ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ ከተጀመረ በኋላ ለማስቆም እና ለማጓተት ከፍተኛ ጥረት ስታደርግ ነበር። ሱዳንን ጨምሮ ሁለቱ ሀገራት በግድቡ አሰራር ሙሌት እና አስተዳደር ስምምነት ላይ ለመድረስ ውይይቶች እና ድርድሮች ሲያካሂዱ ነበር። ነገር ግን በኢትዮጵያ በተከሰተው ፖለቲካዊ ለውጥ ምክንያት ውይይቶቹ ተቋርጠው ከቆዩ በኋላ ከዚህ አመት መጀመሪያ አንስቶ በአዲስ መልክ ተጀምረው ነበር። ሆኖም ድርድሩ ሳይቋጭ ተበትኗል።

የቀደሙትን ለጊዜው ትተናቸው በመጨረሻው ዙር ውይይት ምንድነው የሆነው? የሚለውን እንይ። ከላይ ከጠቀስናቸው የግብጽ ስትራቴጂዎች አንፃር የኢትዮጲያ መንግስት በዚህኛው ዙር ድርድር ምን ስህተት ሰራ?

ድርድሩ መልክ የያዘው ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ እና ፕሬዘዳንት አል ሲሲ በሩሲዋ ከተማ ሶሺ ላይ ከተገናኙ በኋላ ነው። በዚህ በሁለቱ መሪዎች ውይይት ላይ አሜሪካ እና የአለም ባንክ በድድሩ እንዲሳተፉ ተስማሙ። (የተሳትፎ ሚናቸው ታዛቢ ቢባል ቆየት ብሎ ከአደራዳሪም ያለፈ ሆኗል)።

ከዚህ በመቀጠል የሁለቱ ሀገራት ሚኒስትሮች በዋሺንግተን ዲሲ በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ተገናኝተው መደራደር ጀመሩ። የኢትዮጲያ ምሁራን እና ዲፕሎማቶች መጠራጠር የጀመሩት ከዚህ ወቅት ጀምሮ ነው። አድሎዓዊ አቋማቸው በግልጽ እየታወቀ አሜሪካን እና የአለም ባንክን በአደራዳሪነት እንዴት ልንቀበል ቻልን? እንዲህ አይነት ዲፕሎማሲያዊ ስራ ለወትሮው የሚሰራው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆኖ ሳለ ድርድሩ ለምን ወደ ገንዘብ ሚንስቴር ተዛወረ? በተጨማሪም ይህ ድርድር እየተካሄዴ ባለበት ወቅትም አሜሪካ እና የአለም ባንክ ያለወትሮው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለኢትዮጵያ መፍቀዳቸው ተያያዥነት ይኖረው ይሆን የሚሉ ጥያቄዎች በዲፕሎማቶች እና ምሁራኖች መካከል መዘዋወር ጀመሩ።

እንደተፈራውም የስምምነት ውል ተብሎ የተዘጋጀው ሰነድ ለግብጽ የሚወግን እና የኢትዮጵያን መብት እና ጥቅም ክፉኛ የሚጎዳ ሆኖ ተገኘ። ይህንን የተረዱ ዲፕሎማቶች እና ምሁራን በመንግስት አመራር ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደራቸው ተደራዳሪ ልዑካናችን በመጨረሻው ዙር ድርድር ላይ በመቅረት ስምምነቱም ሳይፈረም ቀረ።

ታሪኩ ባጭሩ ይህን ይመስላል። ከግብጽ ጋር አሁን ለገባነው እሰጣ ገባ በር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሳቸው ሳሉ በተቃዋሚዎች ላይ ጣት መቀሰሩ አግባብ ነው? በተናጠል ሩጫው የተሰራውን ስህተት አምኖ ተቀብሎ የጋራ ሀገራዊ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ተቃዋሚን በበንዳነት መፈፍረጅ ያዋጣል?

እንደማጠቃለያ

የአባይ ወንዝ ጉዳይ ለሀገራችን በጣም ወሳኝ የሀገራዊ ጥቅም ጉዳይ ነው። በዚህ አጋጣሚ ይህንን ግድብ የመገደብ ሃሳቡን የጠነሰሱ፤ ወደ ተግባር ለመቀየርም የሚቻላቸውን ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን የተወጡ ያለፉ የቀድሞ መሪዎቻችንና ባለሙያተኞችን እንዲሁም አሁንም ፕሮጄክቱ ፍጻሜ እንዲያገኝ ቀን ከሌት የሚደክሙ ዜጎችን ማመስገን ተገቢ ነው። ይህን ለዘመናት ተነፍገን የነበረውን ጥቅማችንን ለማስከበር ከላይ የጠቀስናቸውን የግብጽ ስትራቴጂዎች ማክሸፍ ወሳኝ ነው። ማለትም፤

1) ይህ ጉዳይ ብሄር፣ ክልል፣ የፖሊቲካ ድርጅት ይቅር እና ሀገራዊ ድንበርን የሚለይ አይደልም። ግብጽ ውሃዉን በበላይነት መያዟ የላይኛው ተፋሰስ ዜጎች፣ ህዝቦች፣ ክልሎች እና ሀገራትን በፅኑ ይጎዳል። ስለሆነም ግብጽ የበላይነቷን ለማስቀጠል የምታደርገውን ጫና ለመቋቋም ሁሉም የላይኛው ተፋፍሰስ ዜጎች፣ ህዝቦች እና ሀገራት መተባበር አስፈላጊ ነው።

2) ከላይ እንደጠቀስኩት የግብጽ ዋነኛ ስትራቴጂ የኢትዮጲያ የውስጥ ፖሊቲካ እና ጸጥታ መታወክ ነው። ይህን ለማክሸፍ ደግሞ የፖሊቲካ ልሂቃኑ ሽኩቻዎች እና ፉክክሮች ወደ ግጭት እንዳያድጉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። ለዚህ ደግሞ የፖሊቲካ ምህዳሩን በማስፋት ልዩነቶች እና ውድድሮች ያለገደብ እንዲሸራሸሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ በዚሁ የለውጥ ጊዜ የፖሊቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ በነበረበት በመጀመሪው አንድ አመት የግብጽ እንቅስቃሴ ቀዝቅዞ ነበር። የውስጥ ፖሊቲካዊ ቀውስ ሲጀምር የነሱም እንቅስቃሴ ጀመረ። ስለዚህ የግብጽን ጫና መቋቋም ከፈለግን የፖሊቲካ ምህዳሩን እያሰፋን መሄድ እንጂ ወደ ቀድሞ አምባገናነአዊ ስርዓት ለመመለስ የሚደርግ ሙከራ የውስጥ ግጭቶችን የሚያስፋፋ እና ተጋላጭነታችንን የሚጨምር መሆኑን መገንዘብ አለብን። ከዚህ አንጻር ገዢው ፓርቲ ከግብጽ ጋር ያለውን ንትርክ ለውስጥ የፖሊቲካ ፕሮፓጋንዳ ለመጠቀም ማሰብ ብሄራዊ ጥቅምን የሚጎዳ መሆኑን ማወቅ አልበት። ሲሆን ሲሆን ሁሉንም የፖሊቲካ ድርጅቶች ጋብዞ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እና ጠንካራ የጋራ አቋም እንዲኖርቻእው ማድረግ እንጂ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ መፈረጅ ለጊዜያዊ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ከተጠቀመ በብሄራዊ ጥቅም ላይ ዘላቂ ጉዳት ያደርሳል።

3) በተለይ በህወሀት/ትግራይና ብልጽግና/ ፈደራል መሃከል እየተካረረ የመጠው ልዩነት ለከፍተኛ ተጋላጭነት ሊዳርገን እንደሚችል እሰጋለሁ። የፖሊቲካ ፍጥጫው ወደወታደራዊ ግጭት ካመራ የውጭ ሀይሎች ጣልቃ ገብነት በሚያስችል መልኩ በራቻንን በርግደን እንደምከፍት መሆኑን ሁሉም ወገን ሊረዳው ይገበል። በተለይ የፌደራል መንግስት ስልጣን የያዙት አመራሮች ይህን የፖሊቲካ ሽኩቻ ከማባባስ ይልቅ ማብረድ አስቸኳይ የቢሄራዊ ድህነንት እና ጥቅም ጉዳይ መሆኑን መረዳት አልባቸው። በኔ ግምት ማንም ለትግራይ ህዝብ የሚያስብ ፓርቲም ሆነ አመራር በአባይ ጉዳይ ላይ ከሌሎች የኢትዮጲያ ሀይሎች የተለየ አቋም ልይዝ አይችልም። የህዳሴው ፕሮጄክት ተግባራዊ ስራ በህወሃት እና መለስ ዜናዊ አመራር ስር የተጀመረ መሆኑ እና የዚህ ፕሮጀክት ስኬት እንደ ትግራይም ሆነ ኢትዮጲያ ኩራታቸው ነው ባይ ነኝ። በሌሎች ጉዳይ እንኳን ቢለያዩ ሀወሀት እና ብልጽግናዎች በግድቡ ጉዳይ ሊያለያያቸው የሚችል አንኳር ነገር ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን የሁለቱ ወደ ከፋ ግጭት መግባት የጋራ ፕሮጄክትን የሚጎዳ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። ስለዚህም በሁለቱም ወገንን ፕሮጀክቱን መነታረኪያ ማድረጉ አይጠቅምም። በነገራችን ላይ አንዳንድ የህውሃት ባለስልጣናት በስሜት እየሰበኩት ያለው ነጻ ሃገረ ትግራይ የመመስረት ህልም እንኳ ቢሳካ የህዳሴ ግድብ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የትግራይን ህዝብ ወደፊት የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይሆንም። እንኳን የኢትዮጵያ አካል የሆነው (ሆኖ የቆዬው) ሌሎች ጎረቢት ሃገራትም እንኳ ከኢትዮጵያ የመበራት ሃይል በአሁኑ ሰዓት እየተጠቀሙ ይገኛል።

4) ሀያላን ሀገራት እና የፋይናንስ ተቋማት ለግብጽ እንደሚያደሉ ግልጽ ነው። ይህ ሰልሆነም በአባይ ጉዳይ ላይ የምናደርገውን ውይይትም ሆነ ድርድር ከነዚህ ሃይሎች ተስታፎ ማራቅ አስፈላጊ ነው። ከዚህ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የሚቀርብልንን እጅ መንሻ እና ማባባያ የፋይናንስ ድግማዎችንም በጥንቃቂቄ ማየት አስፈላጊ ነው።

5) ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር በምናደርገው ግንኙነት የሚያማልል የኢንቨስትመንት ፍስት ቢኖርም በእጀ አዙር በናይል ፖሊቲካ ጉዳይ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ አለብን። ባለፉት ሁለት አመታት በጣም የቅርብ ሽርካችን የሆኑ ሀገራት በሀዳሴው ጉዳይ ከግብጽ ጋር መወገናቸው፤ በድብቅ ምን ያህል ሊያሴሩብን እንደሚችሉ መገንዘብ አዳጋች አይደለም።

6) በዚህ በመጨረሻው ዙር የአባይ ድርድር ላይ ከላይ የጠቀስናቸውን ስህተቶች በመፈጸማችን ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈት እየደረሰብን መሆኑን ማመን አላብን። ሶሺ ሩሲያ ላይ አሜሪካ እና አለም ባንክል እንዲሳተፉ ስንፈቅድ ሱዳን ሳናማክር እና ሳናሳትፍ መሆኑ ሱዳኖችን አስክፍቶ አሁን ከግብጽ ጋር እንዲቆሙ ከፍትኛ ሚና ተጫውቷል። ስለሆነም ከእንግዲህ በምናደርጋቸውን ድርድሮች ላይ ሌሎች አፍሪካ ሀገራትን፣ በተላይ የላይኛው ተፋሰስ ተካፋዮችን፣ ማካተት አስፈላጊ ነው።

7) ባለፉት ሁለት አመታታ የሀገርችን ዲፕሎማሲያዊ ስራ ተቋማዊ መሆኑ ቀርቶ የተቅላይ ሚኒስትሩ ገለሰባዊ (personal ) ተግባር መሆኑን ሁሉም የሚታዘበው ነው። የሀገሪቷን ዲፕሎማሲ እንዲያቀናጅ እና እንዲመራ ሀላፊነት የተሰጠው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደጎን ተገፍቶ ታዛቢ ሆኗል። በዚህ በግድቡ ድርድር እንኳ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እና ወሃና እነርጂ ሚኒስቴር ቀጥሎ የሶስተኛ ደረጀ ተሳትፎ ነው ያለው። ይህ ደግሞ እውቀት እና ልምድ ጠገብ የሆኑ ዲፕሎማቶች እና ባላሙያዎችን አቀናጅቶ ለማሰማራት አዳጋች ስልሆነ ለዲፕሎማሲያዊ ሽንፈታች ጉልህ ሚና አለው። ስለሆነም፣ ወጪ ጉዳን ሚኒስቴርን መለሶ ማጠናከር እና በህግ የተሰጠውን ስልጣን እና ሀላፊነት በሙሉ አቅሙ እንዲጠቀም ለማድረግ ጣልቃ ገብነትን ማሳነስ የስፈልጋል። በሌላ አባባል የሀገርችን ዲፕሎማሲ ከግለሰባዊነት ወደ ተቁማዊነት መመለስ እና መጣናከር ይህን ከግብጽ ጋር የገባንበትን ንትርክም ሆነ ሌሎች ጉዳዮችን በአሸነፊነት እንድወጣ ወሳኝ ነው።

8) ግድቡን በርብርብ በአጭር ጊዜ የምንጨርስበትን መንገድ መቀየስ አስፈላጊ ነው። እንደግለሰብም ሆነ እንደፓርቲ ለዚህ ስኬት ማንኛውንም የምንችለውን ርዳታ ለማድረግ ፍቃደኛ ነን።

ባጠቃላይ የአባይ ወንዝ ጉዳይ በጣም ትልቅ የሀገራዊ ደህነንት እና ጥቅም ጉዳይ ነው። ከማንኛውም የውስጥ ልዩነት የበለጠ። አባይን የሚያክል ጉዳይ ለውስጥ ፖሊቲካ ፍጆታ ማዋልም ከፍተኛ ስህተት ነው። ሰሞኑን የመንግስት ባለስጣናት ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ‘ባንዳ’ የሚል ቃል መጠቀም ጀምረዋል። እውነትም የሀገርን ጥቅም አሳልፎ ከግብጽ ጋር የተሻረከ ሀይል ካለ ከነመረጃው ቀርቦ ፖሊቲካዊ እና ህጋዊ ኪሳራ ሊደርስበት ይገባል። ያላንዳች መረጃ እና የተወንጃዩን ማንነት በግልጽ ሳያስቀምጡ እንደዚህ አይነት ቃላትን መጠቀም አደኛ ነው። የውስጥ ክፍፍልን በማስፋት ለውጭ ሃይል በር ከማስፋትም ባለፈ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያሉ ተቃውሞ እና ትችቶችን ለማፈን በር ይከፍታል። ትላንት ከመለስ መራሹ መንግስት ጋር በመጠፋፋት ደረጀ እየተጋጨንም በነበርንበት ወቅትም ቢሆን፣ በህዳሴ ግድብ ጉዳይ አብረናቸው እንደቆምን ሁሉ፣ አሁን ካሉት የመንግስት መሪዎች ጋርም፣ የውስጥ የፖሊቲካ ልዩነቶቻችንን እንደያዝን ለሀገራችን ብሄራዊ ጥቅምን እና ደህንነት ወሳኝ ለሆነው ጉዳይ የምንችለውን እና የሚጠበቅብንን ሀላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን።

ጃዋር መሃመድ
ግንቦት 3, 2012