“የኖቤል ሽልማት አሸናፊው ጠቅላይ ሚንስትር አዲስ አበባን የመለወጥ እቅድ”

construction project

በሀገራችን የተከሰተውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ ወደመንበረ ሥልጣን የመጡት መሪዎች ባለፉት ሁለት ዓመታ በርካታ የዲዛይ እና የግንባታ ፕሮጀክቶችን አስተዋውቀዋል፡፡ አብዛኞቹ በግንባታ ሂደት ላይ ሲሆኑ የተቀሩት በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡

በግሌ ደጋግሜ እንዳነሳሁት ለውጡን የሚመሩት ኃይሎች ለሀገር እና ለወገን የሚጠቅሙ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ማስተዋወቃቸው በእጅጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡ ምናልባትም ወደፊት ይህንን የለውጥ ወቅት የምናስታውስባቸው (የዘመን መለያ) ፕሮጀክቶች እንደሚሆኑ ይታየኛል፡፡

ዘጋርዲያን (The Guardian) “የኖቤል ሽልማት አሸናፊው ጠቅላይ ሚንስትር አዲስ አበባን የመለወጥ እቅድ” በሚል ርእስ ባለፈው ሰሞን ዋና ዋና የሆኑትን ፕሮጀክቶች በመዘርዘር የኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን አስተያየት አስነብቧል።

በግንባታ ላይ ያሉት እና በዝግጅት ላይ ያሉት ፕሮጀክቶች የሚከተሉት ናቸው።

1) የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ እድሳት
– በጀት – አልተገለጸም
– ሥራ ተቋራጭ – አልተገለጸም

2) የታላቁ ቤተመንግሥት (አንድነት ፓርክ) እድሳት እና ፓርክ
– በጀት – 5 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – ኤሜሬቶች

3) ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት
– በጀት – 31 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – ቻይና

4) የአዲስ አበባ መዘጋጃ ቤት እድሳት
– በጀት – 2 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – ከዱባይ

5) የፒያሳው የአድዋ ማዕከል
– በጀት – 156 ሚሊዮን (ዶላር)
– ሥራ ተቋራጭ – ቻይና

6) የስብሰባ ማዕከል
– በጀት – 10 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – አልታወቀም

7) የአዲስ አበባ ቤተመጻሕፍት
– በጀት – 2 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – ቻይና

8) አዲስ ነገ (Addis Tomorrow )
– በጀት – 3 ቢሊዮን ዶላር
– ሥራ ተቋራጭ – ቻይና

9) አዲስ አፍሪካ የስብሰባ ማዕከል
– በጀት – 2.7 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – አልታወቀም

10) አንድነት ፓርክ የመኪና ማቆሚያ
– በጀት – 2.5 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – ቻይና

11) መገናኛ የትራነስፖርት ተርሚናል
– በጀት – አልታወቀም
– ሥራ ተቋራጭ – አልታወቀም

12) መሶብ ታወር
– በጀት – 681 ሚሊዮን ዶላር
– ሥራ ተቋራጭ – አልታወቀም

13) እንጦጦ ፓርክ
– በጀት – 1.5 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – አልታወቀም

14) ከመዘጋጃ ቤት – ለገሀር – መስቀል አደባባይ መልሶ ማልማት
– በጀት – 2.5 ቢሊዮን ብር
– ሥራ ተቋራጭ – ቻይና

15) ለገሀር መንደር (ሪልስቴት)
– በጀት – 1.9 ቢሊዮን (ዶላር)
– ሥራ ተቋራጭ – ከዱባይ

(ይህ እንግዲህ ASTU ዩኒቨርሲቲ በ30,000,000.00 ዩሮ እገነባዋለሁ ያለውን የሳተላይት መገጣጠሚያ እና ሌሎች በየቦታው የተጀመሩ በርካታ የዲዛይን ግንባታ (Design Build) ፕሮጀክቶች ሳይጨምር መሆኑ ነው።)

ይሁን እንጂ ከፕሮጀክቶቹ ግዙፍነት፣ ከሚፈስባቸው ከፍተኛ በጀት (የተወሰነው በእርዳታ እና በብድር የተገኘ) እና ከፍተኛ ሀገራዊ አጀንዳነት አንጻር ፋታ አግኝተን የተሻለ የሙያተኞች ሀሳብ በመሰብሰብ በቂ ውይይት ለማድግ እና ጽንሰ ሀሳቦቹን ለማበልጸግ አልታደልንም፡፡

ከዚህ በታች የማቀርበው አስተያየት ሀገሩን እንደሚወድ ባለሙያ ዜጋ ብቻ ነው። አንድም የጠቅላይ ሚንስትሩን እና የምክትል ከንቲባውን ቅን ሀሳብ (Good Intention) በመገንዘብ ሊሻሻሉ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ብቻ ይሆናል።

አስተያየቶች ለምን ይሰጣሉ ?

ፕሮጀክቶቹ መደበኛውን የመንግሥት የአገልግሎት ግዢ መመሪያ እና ሳይንሳዊ የፕሮጀክት ትግበራ መንገድ ተከትለው ወደ መሬት ባለመውረዳቸው ጎራ አስለይተው ማወዛገባቸው ቀጥሏል።

እንዳንድ ጭፍን ደጋፊዎች ምንም ሙያዊ አስተያየት ላለመቀበል ጆሮዎቻቸውን በጥጥ ሲደፍኑ ሌሎች ደግሞ ዶ/ር ዐብይ እና አመራራቸውን በታሪክ አጥፊነት እና በ “ተረኝነት” ለመክሰስ ተመችቷቸዋል። የተቀሩት ጥቂቶች ደግሞ ሥራዎቹ የአርኪቴክቸር፣ የከተማ ፕላን እና ምህንድስና ጉዳይ መሆናቸውን ዘንግተው ፖለቲካዊ መልክ በመስጠት “የመታገያ አጀንዳ” እስከማድረግ ደርሰዋል።

ምን ማድረግ ይቻል ነበር ?

 1. ቅደም ተከተል (Priority)
  ከላይ ከተዘረዘሩት 15 ፕሮጀክቶች ከሀገራችንም ሆነ ከከተማችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አንጻር ቅድሚያ የሚሰጣቸው (አንገብጋቢዎቹ) የትኞቹ እንደሆኑ አስቀድሞ በጥናት ሊለዩ ይገባ ነበር። በእኔ አስተያየት ከአንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ይልቅ የከተማዋን የመሠረተ ልማት ችግሮች (የውሃ፣ የመብራት እና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን) እና የኸጣቶችን ሥራ አጥነት ችግሮችን መፍታት ቢቀድም እመኝ ነበር።
 2. አዋጭነት (Feasibility)
  አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች በተነጻጻሪ የሚኖራቸው ጥቅም ከሚፈስባቸው ሀብት አንጻር ሊሞገቱ ይገባ ነበር።
 3. ባለድርሻዎች (Stakeholders)
  እነኚህ ፕሮጀክቶች ለህዝብ እና ለሀገር የሚገነቡ እንደመሆናቸው መንግሥት ብቻውን የሚወስንባቸው መምሰላቸው ትልቅ ጉድለት ነው። በርካታ ሀሳቦቻቸው እንዲካተቱላቸው የሚፈልጉ የሚያገባቸው አካላት ምክራቸው በወጉ ቢካተት ፕሮጀክቶቹን ያግዛል እንጂ ምን ይጎዳል? ዲዛይነሮች፣ ፕላነሮች፣ የታሪክ ባለሙያዎች፣ ቤተእምነቶች ምንም አይመለከታቸውም? አጨብጭቦ ከመቀበል ያለፈ ሚናስ የላቸውም?
 4. የዲዛይን ዝግጅት
  በግሌ ስለዚህ ጉዳይ መጻፍ በራሱ የመታከት ስሜት ይሰማኛል። ነገርየው አውቆ የተኛን ለመቀስቀስ መሞከር ይመስላል። ከታክስ በተሰበሰበ ጥሪት እና በሀገር ስም በልመና የተገኘን በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ለትውልድ የሚቆይ ዲዛይን ለማዋለድ “ጊዜ የለንም” ብሎ መጣደፍ የዚህ ዘመን አመራሮች የወደፊት ጸጸት የሚሆን ይመስለኛል። (ሜቴክን አብጠልጥለን የወቀስነው ለምን ሆነና?) ስም መጥቀሱ ለጊዜው ይቆየኝእና አንዳንድ ፕሮጀክቶች እንደነገሩም ቢሆን የለብለብ ዲዛይን እንኳን ሳይኖራቸው ቁፋሮአቸው መጀመሩን አውቃለሁ።
 5. የዲዛይን እና ግንባታ አካሄድ
  መንግሥት ማንኛውንም አገልግሎት የሚገዛበት የግዢ መመሪያ (Public Project Procurement Procedure) እንዳለው ይታወቃል። ከላይ ከተዘረዘሩት 15 ፕሮጀክቶች ለህዝብ በግልጽ ጨረታ መተላለፉ የተነገረው የምኒልክ ቤተመንግሥት አንድነት ፓርክ የመኪና ማቆሚያ ብቻ መሆኑ ይታወቃል።

በእርግጥ የግንባታ ህጉ እጅግ አንገብጋቢ እና የተለየ አካሄድ ለሚፈልጉ ፕሮጀክቶች ከመደበኛው አሠራር ውጪ እንዲሰጡ እንደሚፈቅድ አውቃለሁ። ለዚህ ደግሞ ህጉ ማረጋገጫ (Justification) ማቅረብ ያስገድዳል።

የመፍትሔ ሀሳብ ?

ፕሮጀክቶቹ ከፊሉ ግንባታቸው በተጀመረበት በዚህ ወቅት ቆሞ ከመወቃቀስ (ወይም ከማለቃቀስ) እንዳንዴም ለፖለቲካ አጀንዳነት ከመጥለፍ ይልቅ ‹‹ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል›› እንዲሉ ሊታረም ስለሚገባው የፕሮጀክት አካሄድ በዕውቀት ላይ ተመስርተን እየተከራከርን ፕሮጀክቶቹን ለሀገር እና ለህዝብ እንዲጠቅሙ ወደ መደበኛው የመንግሥት ፕሮጀክት የግጂ መመሪያ አሠራር መመለስ ይዋል ይደር የማይባል አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡

እንዲህ ቢደረግ !!!

1) ፕሮጀክቶቹ ሀገራዊ ዐቅም ለመገንባት ቅድሚያ ይስጡ

በሀገራችን “በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት” እንደሚባለው እነኚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል መልኩ ለውጭ ዜጎች (አብዛኛው ለቻይና) ካምፓኒዎች የተሰጡ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ሥራ ተቋራጮች እና ባለሙያዎች የበዪ ተመልካች ናቸው።

በልጅነቴ ቤታችን ለንግዶች የቡናቁርስ ሳዘግን “ለአባቱ አዳላ” እንዳልባል ፈርቼ አባቴን አለፍኩት። አባቴ እንዲህ ሲል ተረተብኝ። “ሞኝ አሳላፊ (አስተናጋጅ) አባቱን ያልፈዋል።” በገዛ ቤታችን አባቴን ዘልዬ ጎረቤት ማስዘገን እውነትም ሞኝነት ነበር። የሀገራችን አማካሪዎችን እና ሥራ ተቋራጮችን በዚህ ጊዜ ዐቅማቸውን ካላሳደግን እና ልምድ እንዲያገኙ ካላደረግን መቼ ነው የሚያድጉት? ደግሞስ ሥራ ሲገኝ ለቻይና መዋጮ እና ቀረጥ ሲሆን የእኛዎቹን መጠየቅ ፍትሐዊ ነው?

2) ሀገራዊ የአማካሪ ጉባኤ ይቋቋም

ከላይ የዘረዘርኳቸው ዋና ዋና ፕሮጀክቶች የአንድ ግለሰብ፣ የአንድ ፓርቲ ወይንም የአንድ ትውልድ ብቻ አይደሉም። ዘመን ተሻጋሪ ናቸው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ሠፋ ያለ የሙያ ስብጥር፣ የተሻለ ሀሳብ እና የሥራ ልምድ ያላቸው የሀገር ልጆች ባለሙያዎች በጥቆማ (Recommendations) ተመርጠው በብሔራዊ አማካሪነት ቢሰየሙ የመጣንበትን የተሳሳተ መንገድ ለማረም፣ ያለንበትን አሠራር ለማቃናት እና የወደፊቱን መንገድ ለመተለም ልንጠቀምባቸው እንችላለን።

በስብስቡም ውስጥ አርኪቴክቶች፣ የከተማ ፕላነሮች፣ መሐንዲሶች፣ የታሪክ አዋቂዎች፣ የጥበብ ሰዎች፣ ኢኮኖሚስቶች ወዘተ ቢካተቱበት ዘመን ተሻጋሪ ሀሳብ በማበርከት ሀገርን እና መንግሥትን የሚያግዙ ይመስለኛል።

3) ለህዝብ ወቅታዊ መረጃ ይድረስ

አልፎ አልፎ መንግስት ስለ ፕሮጀክቶቹ ያስረዱልኛል ብሎ የሚለቃቸው ተንሳፋፊ ምስሎች (Animations) በተለይ በባለሙያ ዐይን ሲታዩ ትርጉም የማይሰጡ እና የወረዱ ናቸው። አስፈጻሚውንም ያስገምታሉ።

ዋና ዋናዎቹ ፕሮጀክቶችን ብቻ ብንደምራቸው ከ100 ቢሊዮን ብር የሚልቅ ኢንቨስትመንት የሚፈስባቸው ናቸው። ህዝብ ስለ ፕሮጀክቶቹ ይዘት፣ የግንባታ ሂደት እና አፈጻጸም በስሚ ስሚ ከሚሰማ ወቅታዊ (Updated) እና ዝርዝር መረጃ በየወቅቱ ለህዝብ ሊደርስ ይገባል። ካድሬያዊ ሳይሆን ሙያዊ መረጃ!
____________________

– መልእክቱ ጠቃሚ ከመሰላችሁ Share በማድረግ በጨዋነት ተወያዩበት። [FaceBook:Yohannes Mekonnen]